2018 ኦገስት 2, ሐሙስ

ምስጋና ዘፍልሰታ 2010

አብይ ፆም ስንፆም እጅግ ተጨንቀን፣
አብዝተን ስናለቅስ ሽተን ሰላምን፣
አብይ የተባለ ነብይ ተሰጠን፣
በየቀኑ ፍቅር የሚያስተምረን
በመቶ ቀናት ውስጥ መቶ እርቅ አየን፡፡

አባ አባታችን ቅዱስነትዎ፣
እርቀውን ከርመው ናፍቆን ቡራኬዎ፣
እግዜር በራሱ ቀን ላገሮ አበቃዎ፤
እርቁን ተቀበሉት አብዩ እንዳይደክመው፣
መሪውን ያዝ አርጐ ነዳጅ እንዲሰጠው፡፡

አገር ግን ይገርማል ልብ ላይ ስሜቱ፣
መሶብ እንደሞላ የእንጀራ ብዛቱ፣
ማዲጋ እንደሞላ ኩሽና ዘይቱ፣
አገር ግን ይገርማል ልብ ላይ ስሜቱ፣
የጐደለው ኢምንት መስሎ መታየቱ፣
በደስታ በሰላም በጥቂት መርካቱ፣
አገር እንደዚህ ነው ሲሰጥ በረከቱ፡፡

የፍልሰታዋ ፆም እጅጉን ልዩ ነው፣
ቤትህ እርቅ ገብቷል ሁሉ ልብ አንድ ነው፣
ፀሎታችን ፍሬው ብዙው ምስጋና ነው፣
ሰው ሌላ ምን ይሻል አገር ከተሰጠው?
ሰው ሌላ ምን ይሻል አገር ከተሰጠው?