2016 ሴፕቴምበር 6, ማክሰኞ

አሸንዳ

አሸንዳ
የኔ ልጅ አበባ የኔ ነጭ ወረቀት፣
በቴሌቪዥን መስኮት አይታ እንደገባት፣
ቀጤማ አገልድማ የምትጨፍርበት፣
ለአሸንዳ በዓል ባመት አደረሳት፡፡
እኔም በዚሁ መስኮት መረጃ የሰማሁት፣
የከተማው ቧንቧ ውሃ መስጠት ማቃት፣
ያሸንዳን ሌላ ገጽ ስኖር አሳየኋት፡፡
ይሄንን አሸንዳ ቅርስ ነው ያላችሁ፣
የኔን ቤት አሸንዳም አትርሱት ባካችሁ፡፡



2016 ጁን 16, ሐሙስ

አሜን

ግራ ጐኔን ብዬ በምብርክክ ስለምን፣
ልቤንም አግዞት በፍቅር እንዳምን፣
ሲሰጠኝ አውቄ ብያለሁኝ አሜን፡፡
በሳት ተፈትነሽ ነጥረሽ እየወጣሽ፣
ለቤቴ ምሰሶ በቃሉ የሰራሽ፣
የህይወቴን ፋና በፍቅርሽ አበራሽ፡፡
ካንቺ ጋራ መኖር ፍፁም አይሰለችም፣
ቃሌን ተቀበይኝ ያንቺ ነኝ ዘላለም፡፡
አሜን ይሁንልን በበረከት ይሙላን፣
የልጆችን ደስታ ከእድሜ ጋር ያሳየን፡፡

2016 ኤፕሪል 28, ሐሙስ

እግሬን ያጠብክ ለት …

የሰማዩ ንጉስ ከዙፋንህ ወርደህ፣
ጭራሽ አጐንብሰህ እኔነቴን ወደህ
የኔን ልብ ለማግኘት ተራራውን ወጥተህ፣
ለሌቱን በሙሉ ስትፀልይ አብዝተህ፣
ከጥልቁ እንቅልፌ አነቃኝ ፀሎትህ፤

ልቤን ያጢያት ድንጋይ ተጭኖበት ኑሮ፣
ከቦታው አስቶ ቁልቁል አሽቀንጥሮ፣
እንደግሮቼ እመሬት ሲተሻሽ ኖሮ፤

እግሬን ያጠብክ ለት ባንድ ታጠበና፣
የክፋትን ሥሩን ጣለው ነቀለና፡፡