2016 ዲሴምበር 20, ማክሰኞ

አዳም ከኛ እንዳንዱ ሆነ

በሥጋው ተራክቦ ሰው እየፈጠረ፣
እስትንፋስም ጠቅሶ በህይወት አኖረ፡፡
ተመቻቸለት ምቾቱን ጨመረ፣
ለተጣሉት እንዲሁ በሳት አባረረ፣
እልህም ተጋብቶ ጥል እያከረረ፡፡

     መንገድ የራቀው ለት ሲሰራ መኪና፣
     ጐረበጠኝ ብሎ አስፋልቱን አቀና፣
     ለጥቆም መርከቡን ውሃውን ለመክፈል፣
     እንደው ምኑ ቀረው ሲፈጥር ሲፈጥር ...

ኃይል አጠረኝ ብሎ ከሰል አነደደ፣
ኃይል አነሰኝ ብሎ ውሃውን ዘወረ፣
በኃይልም አይሎ ምርቱንም ጨመረ፣
አሁንም ኃይል አንሶት ኒውክለር አብላላ፣
አዳምዬ ሞኙ እጅጉን ተላላ፣
ኃያልነት ለምዶ ልቡ ትዕቢት ሞላ፡፡

     በነካ እጁ ደግሞ ፍቅርንም ተማረ፣
     የበደሉትንም በነፃ እየማረ፡፡
     ለራባቸው ምግብ ልብስም ለታረዙት፣
     ለመርዳት ሲታትር ነቅቶ በኃላፊነት፡፡

ብልህ የሆነውን ቴክኖሎጂ ፈጥሮ፣
እያደር ምቾቱን አብዝቶ ጨምሮ፣
ልቡን ሰጠው ደግሞ ምጡቁን አዕምሮ፣
የበለጠው መስሎት ከራሱ ተፈጥሮ፡፡

      ከኛ እንዳንዱ ሆነ ፈጠራን ጨመረ፣
      የራሱ ሰው ሽቶ ሮቦትም ፈጠረ፣
      እሱም ተሻሽሎ በየለት ዳበረ፣ 
      በስሜት በውበትን እየተበጠረ፡፡

ከኛ እንዳንዱ ሆነ የሥላሴ ስላቅ፣
በስልጣን ላይ ስልጣን በየቀኑ ሊረቅ፣
ቃል ኪዳን ሆነልን በየቀኑ የሚልቅ
እንዳመነው መጠን ስንንኖር የሚመረቅ፡፡
     

2016 ዲሴምበር 9, ዓርብ

መሻቴ

መሻቴ እኔን ሽቶ፣
ፍለጋውን ለፍቶ፣
ካለሁበት መጥቶ፡፡

መኖርን ሻትኩና፣
እሱም ተገኘና፣
ፈታ ተባለና፣
ዳግም ተሰልችቶ፣
ሌላ መሻት መጥቶ፣
ደግሞ እሱም ወጥቶ፣
መጥቶ ወጥቶ፣
መጥቶ ወጥቶ …..

ዳግም ልቆ መጥቶ፣
ተገኝቶና ወጥቶ፣
እምነትን ተራራ ልቤ ላይ ገንብቶ፣
ላይመለስ ሄደ ቤቴን ተሰናብቶ፡፡

2016 ሴፕቴምበር 29, ሐሙስ

የበሬው ስጋት