2017 ጁን 8, ሐሙስ

ለዲቃላው ልጄ

ለዲቃላው ልጄ
አንድ በስልሣዎቹ መጨረሻ አካባቢ የሚገኙ ጐልማሣ ታሪክ ነው፡፡ በትዳራቸው ብዙ አመት የኖሩ ነገር ግን በትዳራቸው ልጅ ስላልነበራቸው ለእሳቸው በገባቸው መንገድ ምስታቸውንም ሳያስቀይሙ የልጅ አምሮታቸውን በድብቅ ወልደው በድብቅ አሳድገው የተወጡ ሰው ናቸው፡፡ የልጃቸውን ንዴት የእሳቸውን እርካታ ታሪክ ሰምቼ ታሪካቸውንና የእሳቸውን ስሜት እንዲህ ከተብኩት፡፡
ከቤቴ አጥቼህ ከውጭ ያገኘሁህ፣
ሙሉ ሰው እያለህ ዲቃላ ያስባልኩህ፤
አዎን ውዴ አለሜ አንተ ያጥንቴ ፍላጭ፣
አዎን የኔ ጌታ አንተ የደሜ ምጣጭ፣
እውነት ነው መውደዴ እራሴን አብዝቼ፣
እንደምሞት ሳስብ መጥፋትን ፈርቼ፣
ከተከበርኩበት ክብር ተፈትቼ፣
አንተን የወለድኩህ ትክክልን ትቼ፣
የልጅነት ፍቅሬን እምነቴን ጐድቼ፣
የግራዋን ጐኔን አንገት አስደፍቼ፡፡

አውቃለሁ አለሜ ይቅር እንዳትለኝ፣
ለኔ ግን ስህተቴ ፍፁም አይሰማኝ፣
አይንህን እያየሁ መኖር ስለሚሰማኝ፤
በልጅነትህ ውስጥ ሁሌ እታደሳለሁ፣
ህይወቴ ሲቀጥል ባንተ ውስጥ አያለሁ፡፡

አዎን ውዴ አለሜ አጥፍቻለሁ በጣም፣
ግና፣ … ዛሬ ላይም ሆኜ ወደኋላ ሳስብ፣
አንተን እያየሁኝ እኔ አልፀፀትም፤
ታዲያ አጠፋሁ ብዬ ልቤ ሳይፀፀት፣
ይቅርታ እንዳልል ሆኖብኛል ምፀት፡፡

እናም የኔ ጌታ የህይወቴ ቅጣይ፣
እድሜ ይስጠንና አንተም አይንህን እይ፡፡