ሰኞ 24 ዲሴምበር 2018

በዘር ጭቃ ቦካ

የአመራር ጥበብ ረቂቅ አስተሳሰብ፣
በልጆችሽ ሃሳብ በየለቱ ሲጠብ፣
የፈላስፎች ሳይንስ ድንቁ ፖለቲካ፣
ጦቢያ ባንቺ ቤት በዘር ጭቃ ቦካ፣
ታዲያ የጨዋ ልጅ እንዴት እርሙን ይንካ!


እጀ ጠባብ ነበር ሱሪ እንኩዋን ስንጠፋ፣
ከታች ጠበብ ብሎ ወደላይ የሰፋ፣
ወይም ቀሚስ ሽንሽን በደንብ የተስፋፋ፡፡

ስልጡን ነው እያልን ለመድን መጥበቡን፣
እጀ ጠባብ ትተን ሙሉ ጠባብ ለመድን፣
አልፈንም በታይቱ እጅጉን ተጣበቅን፡፡

ጠባብ ፋሽን ሲሆን የልብሱስ ባልከፋ፣
ሃሳብ ሲጠብ ግን እጅጉን ከረፋ፡፡

ያፈርሽ ሰው ሆኜ  ጦቢያ እናት አለም፣
ለኔስ አይቀለኝም መልመድ ሌላ አለም፤
አስም አስይዞኛል ጠረንሽ ከርፍቶ፣
ሊገለኝ ይችላል አልፎ ልቤን ጐድቶ፡፡

ለእስራኤል ያልበጀ ዘሬ ዘሬ ማለት፣
ጥላቻ እየዘሩ በትጋት መኮትኮት፣
ጊዜውን ጠብቆ ፍሬውን ለመጋት፣
በየ50 ዓመቱ በጅምላ ለመሞት፡፡

የአመራር ጥበብ ረቂቅ አስተሳሰብ፣
በልጆችሽ ሃሳብ በየለቱ ሲጠብ፣
የፈላስፎች ሳይንስ ድንቁ ፖለቲካ፣
ጦቢያ ባንቺ ቤት በዘር ጭቃ ቦካ፣
ታዲያ የጨዋ ልጅ እንዴት እርሙን ይንካ!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ