2013 ጁላይ 2, ማክሰኞ

ወጣት ሆይ ውጣ

ወጣት ሆይ ውጣ ከእናትህ ቤት፣
በልጅነት አቅምህን ኑሮን ቅመሳት፣
ላብህ እንደሚያኖርህ በጊዜ ማየት፣
እንድታውቅ ይረዳል የኑሮን ብልሃት፡፡

ወጣት ሆይ ውጣ እናትህ ሳይደክማት፣
ብዙ ጊዜ የለህም ኑሮህን ለማድማት
መለስ ብለህ ደሞ እሷን ለመርዳት፡፡

በወላጆችህ ቤት ኑሮ እንኳ ቢሞላ፣
እንዳያዘናጋህ አትበል ወደኋላ፣
ፍቅር ይዟቸው እንጂ አይደሉም ተላላ፡፡

ያንተ ላብ እንዲበልጥ የጐበዙ ወጣት፣
ልብህ እንዲጠነክር ለኑሮ አቀበት፣
ዝቅ ካለው ኑሮ ሲነሱ አይተውት፣
የነገሩህ ታሪክ እነሱ የወጡት፣
ችላ እንዳትለው ይሁንህ እውቀት፡፡

ወጣት ሆይ ውጣ ኑሮን አሸንፈው፣
ዕድልን ተመልከት አይንህ ስር ነው ያለው፣
ጊዜህ የተሻለ የሰለጠነልህ
ክፉ የማታይበት ሰላም የሞላልህ፣
በተልካሻ ምክንያት አይዛባ ህልምህ፡፡

ወጣት ሆይ ውጣ ጉዋደኞችህን ለይ፣
እንዳትደናቀፍ ከመልካም ጉዞህ ላይ፣
እየጀመርክ ብቻ እንዳትሆን አባይ፣
መጽሀፍት ይኑሩህ በየቀን አለሁ ባይ፣
እንደብረት ጠንክር ለእሳትም ሁን ቀይ፣
ከፍታህን ጨምር በየቀን ወደላይ፣
ቀና ላሉ ሁሉ በቀላሉ አትታይ፡፡

ወጣት ሆይ ውጣ ድረስ ካለምክበት
ጊዜ እየገፋ እንዳይመስልህ ቅዥት
በርታ ጠንክርና አሁን ድረስበት፣
አዕምሮህን ይባርክ የሰማዩ አባት፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ