ዓርብ ፣14 ጁን 2013

እንደዚህ ነው ፍቅር

ትላንትና እንደወትሮው ቀዝቃዛና ዝናባማ አየሩ ከሰዓት በኋላም ዘልቋል፡፡ ሆኖም እንደው ዣንጥላ ይዤ ከመውጣቴ የሚደንቅ ነገር በመስሪያ ቤታችን ግቢ ውስጥ ከሩቅ አየሁ፡፡ አንድ በሃያዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ ወጣት የሥራ ባልደረባችን አብረውት የሚሰሩ ባልደረቦቹ መስማት የሌለባቸው በጣም አስፈላጊ የስልክ ጥሪ ይመስለኛል ከቢሮ ውጪ የሚገኘው አረንጓዴ ሳር መሀል ላይ ሆኖ እጅግ ሞቅ ያለ ፈገግታና ሳቅ በተሞላ አነጋገር ይጫወታል፡፡ ዝናቡም ሆነ ብርዱ ትዝ ያለው አልመሰለኝም፡፡ ለጥቂት ሰከንዶች አብሬው ፈገግ ብዬ ተመለከትኩት፡፡ በሱ ወንበር ተቀምጨ አልል ነገር አልተቀመጠም፣ በሱ ቦታ ቆሜ የሱን ስሜት ተሰምቶኝ ደስታውን ስላልቻልኩት በሰው ልጅ አዕምሮ ቋሚ የመረጃ ቋጥ (Hard disk) ውስጥ ሊቀመጥ የሚገባው ስሜት ሆኖ ስላገኘሁት ከዚህ እንደሚከተለው ከተብኩት፡፡

እንደዚህ ነው ፍቅር
ከሆነማ ላይቀር፣
እንደዚህ ነው ፍቅር፣
ከልብ የሚል ቅርቅር፣
ለትዝታ የሚቀር፡፡
የደወለች ለታ፣
ካሳየች ፈገግታ፣
ቀልጄም ከሳቀች፣
ብሎም ካደነቀች፣
አይን አይኔን እያየች
አለም ዘጠኝ ነች፣
ህይወቴ ደመቀች፣
ነፍሴ እየቦረቀች
ልታልፍ ተመኘች፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ