ሊገልህ ምሎ ቢቃጣ፣
አነጣጥሮ ሊስብ ቃታ፣
የሞት ብይን ላንተ ሰዶ፣
ክፉ ስሙን ልቡ ወስዶ፡፡
የነገር እጁን ላንተ ሲሰድ፣
ክፉ ስሙ አይለቅ በእዶድ፤
ቃታና ጥይት ወዳንድ ኣይሄድ፣
አንዱን ስቦ ሌላን መስደድ፡፡
ጠላትህ
ራሱን ጠልቷል ካንተ በፊት፣
ነገር ይዞ … ሲፈተፍት፣
ሊያለብስህ ሲቸኩል አፈር፣
ልቡ በነገር ሲካረር፣
ነገር ቀምሞ ሲያድር፣
ቀኑ እያለፈ ባሻጥር፡፡
ጠላትህ
ምሬት ገብቶ ከልቡ ጥልቅ፣
ነገር ይዞ ሙጥኝ ባይለቅ፣
ጥላቻውን ቢያንቦረቅቅ፣
እንዳይከትህ ከነገር ጥልቅ፣
በእይታህ ከእሱ ልጠቅ፣
እርጋታህን ባክህ ጠብቅ፡፡
ጠላትህ
መስታውትህ ነው የራስ ማያ፣
የእልህ ስንቅ ማቀበያ፣
ያሸናፊነትህ መለኪያ፡፡
ፈጥሮታልና በመልኩ፣
ተስፋ አልቆረጠም አምላኩ፣
አያጠፋውም ጨርሶ፣
ለሱም ይሰጣል ቀን ቆርሶ፣
ልብም ያገኛል ተውሶ፡፡
ያኔ
ታዲያ … አንተም ፣
ተራህን ጠላት እንዳትሆነው፣
ብድር መላሽ ውሎ አድሮ፡፡
ይልቅ ለፍቅር ይቅር በለው፣
በደስታ በፍቅር አቅፈው፤
ያኔ
ይኼው ጠላት ወዳጅህ ነው፣
ከኖረ ወዳጅ የሚበልጠው፣
አምላክ ቀን ሰጥቶ የለወጠው፡፡
እናም
ጠላትህን በራሱ ጥል አትመዝነው፣
ለዚች ቀን ብድር ስጠው፣
በጠላህ ልክ አትጣላው፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ