2017 ሴፕቴምበር 5, ማክሰኞ

ጉም

ይሄ ጉም ምንድነው እንዲህ የተቀናጣ፣
እንደ ፍልቅቁ ጥጥ ፍሬው እንደወጣ፣
ንጥት ጽድት ብሎ በራሱ ቅርጽ ወጣ፡፡


               ወንድምየው ውሃ ያለቅርጽ የወጣ፣
               ይሄ የመሬት ስበት እንዲህ ቅጥ ካሳጣ፣
              ይሄ ካፈር መኖር ጣጣውን ስንወጣ፣
              እኛስ እንዴት እንሆን ወደላይ ስልወጣ?

2017 ጁን 8, ሐሙስ

ለዲቃላው ልጄ

ለዲቃላው ልጄ
አንድ በስልሣዎቹ መጨረሻ አካባቢ የሚገኙ ጐልማሣ ታሪክ ነው፡፡ በትዳራቸው ብዙ አመት የኖሩ ነገር ግን በትዳራቸው ልጅ ስላልነበራቸው ለእሳቸው በገባቸው መንገድ ምስታቸውንም ሳያስቀይሙ የልጅ አምሮታቸውን በድብቅ ወልደው በድብቅ አሳድገው የተወጡ ሰው ናቸው፡፡ የልጃቸውን ንዴት የእሳቸውን እርካታ ታሪክ ሰምቼ ታሪካቸውንና የእሳቸውን ስሜት እንዲህ ከተብኩት፡፡
ከቤቴ አጥቼህ ከውጭ ያገኘሁህ፣
ሙሉ ሰው እያለህ ዲቃላ ያስባልኩህ፤
አዎን ውዴ አለሜ አንተ ያጥንቴ ፍላጭ፣
አዎን የኔ ጌታ አንተ የደሜ ምጣጭ፣
እውነት ነው መውደዴ እራሴን አብዝቼ፣
እንደምሞት ሳስብ መጥፋትን ፈርቼ፣
ከተከበርኩበት ክብር ተፈትቼ፣
አንተን የወለድኩህ ትክክልን ትቼ፣
የልጅነት ፍቅሬን እምነቴን ጐድቼ፣
የግራዋን ጐኔን አንገት አስደፍቼ፡፡

አውቃለሁ አለሜ ይቅር እንዳትለኝ፣
ለኔ ግን ስህተቴ ፍፁም አይሰማኝ፣
አይንህን እያየሁ መኖር ስለሚሰማኝ፤
በልጅነትህ ውስጥ ሁሌ እታደሳለሁ፣
ህይወቴ ሲቀጥል ባንተ ውስጥ አያለሁ፡፡

አዎን ውዴ አለሜ አጥፍቻለሁ በጣም፣
ግና፣ … ዛሬ ላይም ሆኜ ወደኋላ ሳስብ፣
አንተን እያየሁኝ እኔ አልፀፀትም፤
ታዲያ አጠፋሁ ብዬ ልቤ ሳይፀፀት፣
ይቅርታ እንዳልል ሆኖብኛል ምፀት፡፡

እናም የኔ ጌታ የህይወቴ ቅጣይ፣
እድሜ ይስጠንና አንተም አይንህን እይ፡፡

2017 ጃንዋሪ 23, ሰኞ

ዝቅታን ለመድን

እኛ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ህዝብ ነበርን፣
ዘመናዊ ትምህርት ግራ ሳያጋባን፤

የነዚ ነፃ አውጪ የነዛ ነፃ አውጪ፣
ሁልጊዜ ፍጭት ሁሌ ነገር ጠጪ፤

ጠቃሚ ሃሳብ ሲገኝ የሚሆነን ለለውጥ፣
በሰላም አንችልም ሳይሆንብን ለነውጥ፣
የተሻለ ነገር ተነግሮን አንሰማ፣
በሳት የመጣውን ክፉ ነው ስናማ

ጦርነት ደጋግሞን ዝቅ ዝቅ ሲያደርገን፣
ትውልድ ተቆጠረ ድፍን መቶ ሞላን፤
እራስን መናቁ እየደጋገመን፣
ጊዜ ቆጠረና ዝቅታን ለመድን፤

በዚ ነፃ አውጪ ዛሬም በሳት ሲለን፣
ትንሽ ነን አስባለን ዝቅታ አስለመደን፣
በወዲህም ገዢ ጫን አርጐ ሲገዛን፣
በመሃል በጭንቁ ከክር አቀጠኑን፤

ተመሳሳይ ትግል ተመሳሳይ ውጤት እየደጋገመን፣
ትንሽ ነን አስባለን ዝቅታን ለመድን፡፡