2015 ጁላይ 24, ዓርብ

ሞት እንደሌለ አየሁ

አባቴ ሁልጊዜ ኑርልኝ ከጐኔ፣
በክፍ በደጉ እንድትሆነኝ ወኔ፣
ስመረቅ ትምህርቴን እንድትኮራብኝ፣
ስዳር ስሞሸርም እንድትቆምልኝ፡፡

ልጆቼም ይምጡና ይቦርቁ ፊትህ፣
ልፊያቸውም ቻል እስኪዝል ጉልበትህ፣

ልጆቼንም ይዤ መርቀኝ ልምጣና፣
ሳስመርቅ ስድርም ባለም እቤቴ ና፡፡

መቼ ይጠገባል የወላጅ መኖሩ፣
ያሳቅቃል እንጂ የሞት ዙር ማክረሩ፡፡

ልጆቼ ጠየቁ መቼ ይመጣል አሉ፣
ሞተ’ እንዳልላቸው ጠጠረብኝ ቃሉ፤

በቃሉ ተምሬ ከሞት ወዲያ ህይወት፣
ተቀብዬው ኖሬ በልበ-ሙሉነት፣
ዛሬ ባንተ መሞት እምነቴ ሆነ እውነት፤

ከሞትክም በኋላ እንዳለህ ስላየሁ፣
አባቴ ባንተ ሞት - ሞት እንደሌለ አየሁ፡፡

ከሞትክም በኋላ እንዳለህ ስላየሁ፣
አባቴ ባንተ ሞት - ሞት እንደሌለ አየሁ፡፡

አባቴ በሞትህ ዛሬም ተምሬአለሁ፣
ፍቅርህን ሞተህም ዛሬም አየዋለሁ፣
የፍቅር መምህሬ እኔም ‘ወድሃለሁ፡፡

2015 ሜይ 25, ሰኞ

ሂውማን ሄር

በህንድ ሃገር የተራበች፣
ፀጉሯን ሸጣ እየበላች፣
ኑሮን ለዕለት እየገፋች፣
ነገም ሲያድግ እየላጨች፣
የአለሙን ሴት ታስውባለች፡፡

ሂውማን ሄር  - የሰው ፀጉር፣
በብር መጥቶ የሚያምር፣
ላለው ማማር የሚገበር፡፡

የራስ አፍሮ አሳፍሮ፣
ከሰው በታች ሆኖ አሮ፡፡

የራስ ፀጉር ለማሳደግ፣
ጊዜ ይፈጃል አይልም ብድግ፣
ገንዘብ ካለ ሊንዠረገግ፣
የሰው ፀጉር ባለማዕረግ፡፡

የድሃዋ ምሣ መብያ፣
የኔ በየለት መዋቢያ፣
ባናቴ ላይ ተቆልሎ፣
እኔነቴንም ከልሎ፣
እንዳያስረሳኝ ጠቅልሎ፡፡

2015 ጃንዋሪ 27, ማክሰኞ

ለኛ ነው ጨለማ?

ግብር ከፍለን ከፍለን፣
ጊቢን 3 ገድበን፣
አባይንም ደግመን፣
ቦንድ ሁለቴ ገዝተን፣
በየቀኑ A ባልን፣
ገቢዎች በሰማ፣
ለኛ ነው ጨለማ?