2016 ጁን 16, ሐሙስ

አሜን

ግራ ጐኔን ብዬ በምብርክክ ስለምን፣
ልቤንም አግዞት በፍቅር እንዳምን፣
ሲሰጠኝ አውቄ ብያለሁኝ አሜን፡፡
በሳት ተፈትነሽ ነጥረሽ እየወጣሽ፣
ለቤቴ ምሰሶ በቃሉ የሰራሽ፣
የህይወቴን ፋና በፍቅርሽ አበራሽ፡፡
ካንቺ ጋራ መኖር ፍፁም አይሰለችም፣
ቃሌን ተቀበይኝ ያንቺ ነኝ ዘላለም፡፡
አሜን ይሁንልን በበረከት ይሙላን፣
የልጆችን ደስታ ከእድሜ ጋር ያሳየን፡፡

2016 ኤፕሪል 28, ሐሙስ

እግሬን ያጠብክ ለት …

የሰማዩ ንጉስ ከዙፋንህ ወርደህ፣
ጭራሽ አጐንብሰህ እኔነቴን ወደህ
የኔን ልብ ለማግኘት ተራራውን ወጥተህ፣
ለሌቱን በሙሉ ስትፀልይ አብዝተህ፣
ከጥልቁ እንቅልፌ አነቃኝ ፀሎትህ፤

ልቤን ያጢያት ድንጋይ ተጭኖበት ኑሮ፣
ከቦታው አስቶ ቁልቁል አሽቀንጥሮ፣
እንደግሮቼ እመሬት ሲተሻሽ ኖሮ፤

እግሬን ያጠብክ ለት ባንድ ታጠበና፣
የክፋትን ሥሩን ጣለው ነቀለና፡፡

2016 ኤፕሪል 27, ረቡዕ

ክርክም

ክርክም እንደ አትክልት፣
ክርክም እንደ አፍሮ፣
በስግደት መከርከም፣
በጽሞና ማረም፣
በፆም ለመገረዝ፣
ይበቃል መደንዘዝ፣
በኑሮ ላይ መፍዘዝ፡፡

ደግሞም እንበል ቀና፣
ጨመር አርገንበት ፍቅርና ትህትና፣
ልዩነት መኖሩ ይሞላላልና፡፡

ክርክም .. ክርክም … ክርክም ፣
የልቦናን ክፋት በፅሞና እክም፣
የትዕቢትን ነገር በፆም በማዳከም፣
የጉልበትን ግነት በስግደት ማለዘብ፣
ሰዋዊ ድግመትን በፆም መቀስ ክርክም፡፡