2017 ሴፕቴምበር 8, ዓርብ

ፍልስፍና - ዘመድህ አድርገኝ

የዘርዐ ያዕቆብን ፍልስፍና የሚል መጽሐፍ አንብቤ እንደው የነካኝን ማንነቱን የፍቅር መምህርነቱን ከዚህ ትውልድ ጋር እንዲህ አገናዝቤ ከተብኩት፡፡

ዘርዓያዕቆብ ዘረ ስደተኛ፣
እምነት ፍቅር አንሶት ከሆነ ጦረኛ፣
ዘመዶችህን ተውህ ለክፋት ላትተኛ፤
በዋሻ ተደበቅህ ክፉ ቀን እስኪያልፍ፣
ብዙ ኑሮህን ኖርህ በፈጣሪ እቅፍ፡፡

           ጵጵስና ታጨተህ በዋሻ ውስጥ ብትቆይ፣
           ቤተስቲያን ልትኖር የግዚአብሔር አገልጋይ፣
           መቼ አወቁልህ በሰው ናፍቆት ብትጋይ፣
           ነገርን ለመሸሽ ከመንጋው ብትለይ፣
           ከጥላቻ እንጂ ከሰው እንዳትለይ፡፡

 ደግሞም የተጠጋህ ከሃብቱ በሥራ፣
 ለኑሮ የሚበቃ መሆን መረጥህ ተራ፣
 የሃብቱን ደግነት እጅጉን መረጥኸው፣
 የሚልቅን ዋጋ ዝምድናን ጠየቅኸው፡፡
በሃብቱ ዝምድናም እጅጉን ተባረክህ፣
ጐረቤቱም ሆነህ ፍቅር ቤትህን ሰራህ
ዘመዶችህንም በፍቅር ተሰናበትህ፡፡

      ያንተ አርዓያ ዘሩ በርክቶ በዛና፣
      ሁሉም ዘመዶቹን እጅጉን ተወና፣
     ስደትን መረጠ እርቆ ወጣና፡፡

እድሉን ቢሰጠው ሰርቶ እንዲበላ፣
እየተዘመደ ባለም ሁሉ መላ፡፡

2017 ሴፕቴምበር 5, ማክሰኞ

ጉም

ይሄ ጉም ምንድነው እንዲህ የተቀናጣ፣
እንደ ፍልቅቁ ጥጥ ፍሬው እንደወጣ፣
ንጥት ጽድት ብሎ በራሱ ቅርጽ ወጣ፡፡


               ወንድምየው ውሃ ያለቅርጽ የወጣ፣
               ይሄ የመሬት ስበት እንዲህ ቅጥ ካሳጣ፣
              ይሄ ካፈር መኖር ጣጣውን ስንወጣ፣
              እኛስ እንዴት እንሆን ወደላይ ስልወጣ?

2017 ጁን 8, ሐሙስ

ለዲቃላው ልጄ

ለዲቃላው ልጄ
አንድ በስልሣዎቹ መጨረሻ አካባቢ የሚገኙ ጐልማሣ ታሪክ ነው፡፡ በትዳራቸው ብዙ አመት የኖሩ ነገር ግን በትዳራቸው ልጅ ስላልነበራቸው ለእሳቸው በገባቸው መንገድ ምስታቸውንም ሳያስቀይሙ የልጅ አምሮታቸውን በድብቅ ወልደው በድብቅ አሳድገው የተወጡ ሰው ናቸው፡፡ የልጃቸውን ንዴት የእሳቸውን እርካታ ታሪክ ሰምቼ ታሪካቸውንና የእሳቸውን ስሜት እንዲህ ከተብኩት፡፡
ከቤቴ አጥቼህ ከውጭ ያገኘሁህ፣
ሙሉ ሰው እያለህ ዲቃላ ያስባልኩህ፤
አዎን ውዴ አለሜ አንተ ያጥንቴ ፍላጭ፣
አዎን የኔ ጌታ አንተ የደሜ ምጣጭ፣
እውነት ነው መውደዴ እራሴን አብዝቼ፣
እንደምሞት ሳስብ መጥፋትን ፈርቼ፣
ከተከበርኩበት ክብር ተፈትቼ፣
አንተን የወለድኩህ ትክክልን ትቼ፣
የልጅነት ፍቅሬን እምነቴን ጐድቼ፣
የግራዋን ጐኔን አንገት አስደፍቼ፡፡

አውቃለሁ አለሜ ይቅር እንዳትለኝ፣
ለኔ ግን ስህተቴ ፍፁም አይሰማኝ፣
አይንህን እያየሁ መኖር ስለሚሰማኝ፤
በልጅነትህ ውስጥ ሁሌ እታደሳለሁ፣
ህይወቴ ሲቀጥል ባንተ ውስጥ አያለሁ፡፡

አዎን ውዴ አለሜ አጥፍቻለሁ በጣም፣
ግና፣ … ዛሬ ላይም ሆኜ ወደኋላ ሳስብ፣
አንተን እያየሁኝ እኔ አልፀፀትም፤
ታዲያ አጠፋሁ ብዬ ልቤ ሳይፀፀት፣
ይቅርታ እንዳልል ሆኖብኛል ምፀት፡፡

እናም የኔ ጌታ የህይወቴ ቅጣይ፣
እድሜ ይስጠንና አንተም አይንህን እይ፡፡