2014 ኖቬምበር 5, ረቡዕ

ዝም አሰኘኝ

ፍቅሩንም ለመቅመስ፣
ቃሉን ለማወደስ፣
ለመስማት ሲቀደስ፣
ከፍላጐት ንፋስ፣
አደረገኝ ትንፍስ፡፡

ሃሳቤን ሞላልኝ፣
ሁሉ ተሳካልኝ
ፀሎት አለቀብኝ፣
በፈቃዴ አዋለኝ፡፡
በደስታ ቦርቃ
በምስጋናው ልቃ፣
ልቤን ደስ እያለኝ፣
ብቻ ዝም አሰኘኝ፡፡

2014 ሴፕቴምበር 2, ማክሰኞ

ግማሽ ጨረቃ


ግማሽ ነች ጨረቃ ዛሬ የተባልሽው፣
ባለፈው ሰሞን ግን ሙሉ የነበርሽው
ምን ቆረሰሽ ከጐን ምንስ አጐደለሽ?
ወይስ ሙሉነትሽን ማነው የደበቀሽ?

ፀሀይ ሙቀትሽን ስትታጠን አድራ፣
አስባ ተውባ እጅጉንም አምራ፣
ማልዳ ትወጣለች ለአለም ልታበራ፡፡

ጨረቃ ድምቡልቃ ሰው ከተኛ ወጥተሽ፣
ለሱም ኃፍረት ይዞሽ በግማሽ ጐን ወጣሽ፡፡

ፀሀይም ጐንሽን በከፊል ደብቃ
ግማሽ ስትወጪ ማነስሽን ንቃ፣
ሲነጋላት ደግሞ እንድትታይ ልቃ፡፡

ጨረቃ ሙሉ ነሽ ውበትሽ ደማቅ፣
እንቅልፍ ለማይጥለው አንቺን ለሚያውቅ፣
የነፍስ ምግብ ነሽ ሁል ጊዜም ብርቅ፡፡

2014 ፌብሩዋሪ 24, ሰኞ

ውሃን ለፍቅር

የአባይ ተፋሰስ ውሃ ተጣጪዎች፣
ባንድ የተጋበዙ የግዜር ታዳሚዎች፣
ውሃ ከሰማይ ላይ መሆኑን ተረድተን፣
ትብብር ላይ ሆነን አብረን እየሰራን
ተስማምተን ልንጠጣ ባንድ ከተሰጠን፣
በቅናት ነደደ ፍቅር ጠላ ሰይጣን፡፡

ስስትን ዘራና በግብጽ ጋዜጦች፣
ቁጣን ጨመረና በግብፅ የሰው ልቦች፣
መገፋፋት መጣ ወደኃላ ማለት፣
ጠልተውንም ሳይሆን ብቻ ለራስ ማድላት፡፡

የጥል መሠረቱ ነውና ዲያቢሎስ፣
የልቡ አምሮቱ እንድንጨራረስ፡፡
ስልጣኑም ተሰጥቶት ሊፈትን ከጌታ፣
ያናፍስብናል የስስት ጫጫታ፡፡

ቸግሮት አይደለም የሰጠን ባንድ ላይ
እንድንኖር ሽቶ ነው እንዲህ ሳንለያይ፣
ከሰይጣን እንድንበልጥ በደንብ እናውቃለን፣
ለትብብር ለፍቅር እንበረታለን፡፡